ለድህረ ምርጫ ችግሮች መፍትሄዎች ያፈለቁ ወጣቶች ተሸለሙ

ለድህረ ምርጫ ችግሮች የዲጂታል መፍትሄ ለመሻት በአዲስ አበባ በወጣቶች መካከል በተደረገ ውድድር የድረ-ገጽ መተግበሪያ ሰርተው ያቀረቡ አምስት ወጣቶች አሸነፉ። የድረ-ገጽ መተግበሪያው የድምጽ ቆጠራ እና የምርጫ ውጤቶችን ለማሳለጥ የሚያስችል ነው። 

በብሔራዊ ቤተመጽሐፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ግቢ በሚገኘው የአሜሪካ ማዕከል ከአርብ የካቲት 20 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ውድድር በ10 ቡድኖች የተከፋፈሉ በርከት ያሉ ወጣቶች ተሳትፈውበታል። ቡድኖቹ በ48 ሰዓታት ውስጥ ያዘጋጇቸውን “የአፕልኬሽን እና ሃርድዌር” ስራዎቻቸውን ለዳኞች ካቀረቡ በኋላ ሶስት አሸናፊዎች ተለይተዋል። 

ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቁት “ባቡን ቴክ” በሚል ስያሜ ለውድድር የቀረቡ ወጣቶች ናቸው። ሶስት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ያካተተው ይሄው ቡድን በድህረ ምርጫ ወቅት ስለሚያጋጥሙ ችግሮች በውድድሩ አዘጋጆች በኩል የቀረበውን ገለጻ በመንተራስ መፍትሄ ለማበጀት ሞክሯል። የቡድኑ አባል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ሄኖክ ዘላለም ለ”ኢትዮኢሌክሽን” እንደተናገረው እነሱ የሰሩት ስርዓት በድህረ ምርጫ “የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚፈታ” እና “ሰዓትን መቆጠብ” የሚያስችል ነው።

ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቁት “ባቡን ቴክ” በሚል ስያሜ ለውድድር የቀረቡ አምስት ወጣቶች ናቸው

የ21 ዓመቱ ሄኖክ “እኛ የሰራነው ዌብ አፕልኬሽን ነው። ለዌብ አፕልኬሽኑ ሶስት አይነት ደረጃ አዘጋጅተንለታል። አንደኛ ታች ምርጫ ጣቢያ ያሉ ሰዎች አሉ። በመሀል ደግሞ constituencies [የምርጫ ክልሎች] የሚባሉ እነሱን ይቆጣጠራሉ። ከዚያ ደግሞ የምርጫ ቦርድ ዋናው ጽህፈት ቤት አለ። ያንን አካሄድ ተከትሎ ማጭበርበር ሳይፈጠር፣ ወጪ በማያስወጣ መልኩ እንዴት ላይ ይደርሳል የሚለውን ነው የሰራነው” ሲል ለአሸናፊነት ያበቃቸውን ስራ ምንነት አስረድቷል። 

በውድድሩ ሁለተኛ እና ሶስተኛ የወጡት ቡድኖች “ሃርድዌርን እና ሶፍትዌርን” ቀላቅለው ያቀረቡ ናቸው። ውድድሩን የማስተባበር ሚና በወሰደው “ጉግል ዴቨሎፐርስ ግሩፕ” በተሰኘ የኮዲንግ ባለሙያዎች ስብስብ ውስጥ በኃላፊነት የሚሰራው መላክ ውብሸት ወጣቶቹ የሰሯቸው ስራዎች “ጥንቃቄ የተሞላበት ቆጠራ ለማካሄድ” የሚያስችሉ እንደሆነ ለ”ኢትዮኢሌክሽን” ገልጿል።

ለድምጽ ቆጠራ ላፕቶፖችን ከመጠቀም ይልቅ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ እና እዚሁ ሀገር የሚሰሩ ትንንሽ የመቆጣጠሪያ ቦርዶችን አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚቻል ወጣቶቹ በተግባር ማሳየታቸውንም አስረድቷል።

መላክ ውብሸት ወጣቶቹ የሰሯቸው ስራዎች ከ48 ሰዓት ባነሰ ጊዜያት ውስጥ የሰሯቸው “ትልቅ የሚባሉ ስራዎች ናቸው” ይላል

“አንድ ሰው የመረጠበትን የድምጽ መስጫ ወረቀት [ወጣቶቹ] ለሰሩት ሃርድዌር ስትሰጠው ይሄኛው ተቀባይነት ያለው ነው አይደለም? የተበላሸ ነው አይደለም? የሚለውን ማረጋገጫ ይሰጣል። ትክክል ከሆነ ደግሞ የትኛው ፓርቲ እንደተመረጠ ወዲያውኑ አውቆ እዚያ ፓርቲ ላይ ድምጹን ይጨምርለታል” ሲል መላክ አሰራሩን ያስረዳል።  

በአሜሪካ ኤምባሲ አዘጋጅነት እና አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህን መሰል የወጣቶች የዲጂታል መፍትሄ ፍለጋ ውድድር ሲካሄድ የአሁኑ ለስምንተኛ ጊዜ ነው። የአሁኑን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ጊዜያት የተካሄዱት ውድድሮች ማጠንጠኛቸው ያደረጉት ምርጫን ነበር። ቀደም ሲል የተካሄዱት ሁለት ውድድሮች በመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ መስጫ ቀን ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄዎች ቀርበውባቸዋል። 

እነዚህ መፍትሄዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚችሉ የሚያምነው የውድድሩ አስተባባሪ መላክ ውብሸት ወጣቶቹ የምርጫን ጉዳይ ከሚከታተሉ ኃላፊዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት “ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ይላል። “አሁን ያሸነፉት ልጆች ያመጡት ሃሳብ እና መፍትሄዎች ተንጠልጥለው ነው የቀሩት። ወደ መሬት ለማውረድ የተለያዩ አካላት እገዛ ያስፈልጋል” ሲል አጽንኦት ይሰጣል።

ስለ ወጣቶቹ እንቅስቃሴ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶልያና ሽመልስ “እንዲህ አይነት ጥረቶችን ቦርዱ ያበረታታል” ሲሉ ለ”ኢትዮኢሌክሽን” ምላሽ ሰጥተዋል። “ከምርጫ ጋር በተገናኘ በማንኛውም መልኩ በጎ ፍቃደኛ መሆን የሚፈልጉ እንዲመዘገቡ ጠይቀናል” ሲሉም በቦርዱ በኩል ለእንዲህ አይነት ተነሳሽነቶች ያለውን በጎ አመለካከት ጠቁመዋል።

Leave a Reply