- አራት የፓርቲዎች ስብስቦች የቅንጅት ጥያቄያቸውን ለቦርዱ አቅርበዋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ መሳተፍ ለሚፈልጉ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጠው ቀነ ገደብ ውስጥ የተመዘገቡት ስድስት ብቻ መሆናቸውን ገለጸ። የቅንጅት መመስረቻ ማመልከቻቸውን በቀነ ገደቡ ያሳወቁ የፓርቲ ስብስቦች አራት ብቻ መሆናቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።
የሃያ ሁለት አዲስ ፓርቲዎችን የምዝገባ ማመልከቻ እየተመለከተ የሚገኘው ምርጫ ቦርድ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ለሚፈልጉ ተመሳሳይ አመልካቾች እስከ ትላንት ሰኞ፣ የካቲት 30፣ የሚቆይ ቀን ገደብ ሰጥቶ ነበር። ቦርዱ ቀነ ገደቡን ያስቀመጠው “ለመጪው ምርጫ ፓርቲዎችን ብቁ የማድረጉ ስራ ጊዜ የሚወስድ” መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሶ ነው።
በምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሰነዶች አሟልተው ለመስሪያ ቤቱ ያስገቡ ስድስቱም አዲስ ፓርቲዎች በክልል እና ከተማ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በክልላዊ ፓርቲነት ለመመዘገብ ማመልከቻቸውን ያስገቡት በሶማሌ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር እና አማራ ክልሎች እንደዚሁም በድሬዳዋ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ናቸው።
ምርጫ ቦርድ ከየካቲት 30 በኋላ የምዝገባ ማመልከቻቸውን የሚያስገቡ አዲስ ፓርቲዎች ከመጪው ምርጫ ውጪ እንደሚሆኑ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቁ ይታወሳል። ቦርዱ ግንባር አሊያም ቅንጅት መመስረት ለሚፈልጉ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር።
የቀነ ገደቡ ዕለት ሳያልፍ የቅንጅት ማመልከቻቸውን ለመስሪያ ቤቱ ያስገቡ የፓርቲዎች ስብስቦች አራት ብቻ መሆናቸውን ቦርዱገልጿል። መቀናጀታቸውን ለምርጫ ቦርድ ካሳወቁት ውስጥ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ይገኙበታል። “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት” የተሰኘው የሶስት ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ስብስብም ለቦርዱ የቅንጅት ጥያቄ ካቀረቡት መካከል መሆኑን ቦርዱ አረጋግጧል።
“አብሮነት” በተሰኘው መጠሪያ የሚታወቀውን ይህን ቅንጅት የመሰረቱት የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር-ኢትዮጵያ) የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። ፓርቲዎቹ በመጪው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀናጅተው ለመስራት መስማማታቸውን ለቦርዱ ባስገቡት ማመልከቻ ላይ ጠቁመዋል።
ከቀነ ገደቡ ሶስት ቀናት አስቀድመው መቀናጀታቸውን ይፋ ያደረጉት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም (መኢአድ) ማመልከቻቸውን ለቦርዱ አስገብተዋል። “ባልደራስ መኢአድ” የሚል መጠሪያ እንደሚጠቀሙ ያስታወቁት ፓርቲዎቹ በመጪው ምርጫ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ፤ በጋራ የምርጫ ማኒፌስቶ እና ምልክት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል። (ኢትዮኢሌክሽን)