የምርጫ ክልሎች ካርታ ይፋ ተደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልል ካርታን ዛሬ ይፋ አድርጓል። በዛሬው ስነ ስርዓት ላይ የሀገር አቀፍ፣ የዘጠኙ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ክልል ካርታዎች ለዕይታ በቅተዋል።

በአዲስ አበባው ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በተካሄደው በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ክልሎች ካርታን በተመለከተ በመስሪያ ቤታቸው ስለተደረገው ዝግጅት ማብራሪያ ሰጥተዋል። “አሁን የምርጫ ቦርድ ያደረገው የምርጫ ክልልን እንደገና ማካለል ወይም ማሻሻል አይደለም። ተበታትኖ የነበረውን የቃላት የካርታ መረጃ፤  በዘመናዊ መልክ አሰናድቶ፤  ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ካርታነት መለወጥ ነው” ሲሉ ለተሰብሳቢዎች አስረድተዋል። 

በስነ ስርዓቱ ላይ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ “የምርጫ ክልሎች አከላለል መርሆዎች እና ህጋዊ ማዕቀፉን” የተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል። የምርጫ ክልል “የሕዝብ ተወካዮች የሚመረጡበት፣ የተወሰነ የህዝብ ቁጥር የያዘ፣ ተለይቶ የሚታወቅ እና ከሌሎች የምርጫ ክልሎች ጋር የሚዋሰን አካባቢ” እንደሆነ ገልጸዋል። በአንድ የምርጫ ክልል እንደ የሀገሩ ሁኔታ አንድ አሊያም ሁለትና ከዚያ በላይ ተወካዮች ሊመረጡ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። 

“አንድ የምርጫ ክልል ምን ያህል ህዝብ ነው መያዝ ያለበት?” የሚለው አለም አቀፍ መለኪያ ማስቀመጥ እንደማይቻል ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል። በአሜሪካ የምርጫ አወካከል 800 ሺህ ህዝብ አንድ ተወካይ እንዳለው ያስታወሱት የህግ ምሁሩ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት አንድ ተወካይ ስንት ሰዎች መወከል ይገባው እንደነበር ጥቆማቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት የተቀመጠው የፓርላማ መቀመጫ ብዛት 550 መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ጌታቸው መቀመጫው ለህዝብ ብዛት ሲካፈል፣ አንድ ተወካይ ከ180 ሺህ እስከ 190 ሺህ ሊወክል ይገባው እንደነበር ስሌቱን አስቀምጠዋል። 

የምርጫ ክልሎች አከላለል ታሪካዊ ዳራን ያብራሩት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ 100 ሺህ የሚደርስ የህዝብ ብዛት ያላቸው እንደ አንድ የምርጫ ክልል ይወሰዱ እንደነበር ገልጸዋል። የዚህንም አፈጻጸም ሲፈትሹ ችግሮች እንደታዩበት አስረድተዋል። የምርጫ ክልሎች የተካለሉት ለህገ መንግስት አጽዳቂ ጉባኤ ዝግጅት በተቋቋመ ግብረ ኃይል በ1985 ዓ.ም. እንደነበር የተናገሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ያለፉት አምስት ምርጫዎች የተካሄዱት ግብረ ኃይሉ ባካለላቸው 547 የምርጫ ክልሎችን እንደሆነ አመልክተዋል። ግብረ ኃይሉ የምርጫ ክልሎችን ለማካለል የተጠቀመው የህዝብ ቆጠራ ውጤት ግን በደርግ ጊዜ በ1976 ዓ.ም. የተደረገውን ነበር ብለዋል።   

ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎችን እንደገና እንዳላካለለ የተናገሩት ብርቱካን ሚደቅሳ የዘንድሮ ምርጫ በቀድሞዎቹ የምርጫ ክልሎች እንደሚካሄድ ግልጽ አድርገዋል። የምርጫ ክልሎችን እንደገና ማካለል ወይም ማሻሻል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት፤ ይህም ስድስት ወር ሊወስድ እንደሚችል ያነሱት የቦርድ ሰብሳቢዋ ምርጫውን በጊዜ ለማካሄድ እንደማያስችል አስረድተዋል። የህዝብ እና ቤት ቆጠራ በወቅቱ አለመካሄዱም እንደገና ላለማካለሉ ሌላው ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል። 

በስነ ስርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲከኞች ከምርጫ ክልሎች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አቅርበዋል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) ስራ አስፈጻሚ አባል ሀሰን ሙአሊም፤ የምርጫ ክልል ካርታው የሶማሌ ህዝብ ክልልን በሚመጥን መልኩ እንዲሻሻል ሀሳብ አቅርበዋል። ሌላ ተሳታፊም “የክልሎችን የካርታ ወሰን የጠበቀ አይደለም” ብለዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ምርጫ ቦርድ የቆየ መረጃ ለምን ተጠቀመ? ብለዋል። አቃቂን በምሳሌነት በማንሳት በፊት በአንድ ክልል የነበሩ ወደ ሌላ መካተታቸውን አንስተዋል። በምርጫ ክልል ካርታዎች ውስጥ ሲዳማ በክልልነት ለምን እንዳልተካተተም ጠይቀዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ “የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ስራውን ጨርሷል። የስልጣን ርክክቡ ተፈጽሞ፤ ሲዳማ ክልል መሆኑ formalize ካልተደረገ፤ ለፓርላማ መቀመጫ ቆጥረን ማቅረብ አይጠበቅብንም። ብናደርግም ስህተት ነው” ሲሉ መልሰዋል። 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ዛሬ ይፋ በተደረገው የምርጫ ክልሎች መሰረት በሁሉም ቦታዎች ምርጫ ይካሄድ እንደው ጠይቀዋል። ብርቱካን ሚደቅሳ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ” ‘ምርጫ በዚህ ቦታ አይደረግም’ ብለን የያዝነው የምርጫ ክልል የለንም። በሀገሪቱ በሙሉ ለማከናወን ነው ያቀድነው። ከባድ ጎርፍ፣ እሳት፣ ከባድ የጸጥታ ችግር፤ ምርጫ ለመከወን ካስቸገረን፤ የዚያን ጊዜ የምናየው ይሆናል” ብለዋል። 

በዛሬው የምርጫ ክልል ካርታ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም ተገኝተዋል። (ኢትዮኢሌክሽን)

Leave a Reply