መጪው ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በታቀደለት ጊዜ እንደማይካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት መጪውን አጠቃላይ ምርጫ ማድረግ የማይችል መሆኑን አስታወቀ። የተወካዮች ምክር ቤት ሁኔታውን ተገንዝቦ ውሳኔ እንዲያሳልፍም ጠይቋል።

ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በምርጫ 2012 ኦፕሬሽን ላይ የፈጠረውን ችግር ከገመገመ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ ባለፈው የካቲት ወር ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረዙን ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳው የታቀዱ ተግባራትም ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑንም ገልጿል።

በቦርዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲሆን ታቅዶ ነበር። ቦርዱ ከምርጫው ማግስት አንስቶ እስከ ጳጉሜ 3 ድረስ የተረጋገጠ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ በጊዜ ሰሌዳው ማስቀመጡ ይታወሳል።

በተለምዶ በግንቦት ወር ይካሄድ የነበረው አጠቃላይ ምርጫ ወደ ነሐሴ ወር የተገፋው በአዲስ አወቃቀር እና አባላት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመጪው ምርጫ “በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዲያገኝ” በሚል ነበር። ምርጫው በክረምት ወር እንዲደረግ መወሰኑን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። 

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ መጪውን ምርጫ ከነሐሴ ወር ወዲያ ባሉት ጊዜያት ለማከናወን የማይችለው በኢትዮጵያ ህገ መንግስት በተቀመጠ ገደብ ምክንያት መሆኑን ምላሽ ሰጥቶ ነበር። ቦርዱ በዛሬው መግለጫውም ይህን የህገ መንግስት የጊዜ ገደብ አንስቷል። 

በስራ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ መጪውን አጠቃላይ ምርጫ ማድረግ እንደሚኖርበት መግለጫው አስታውሷል። ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት እንዳያከናውን ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል። በዚህም ምክንያት ምርጫውን በእቅዱ መሰረት ማድረግ እንደማይችል አስታውቋል።

የተወካዮች ምክር ቤት አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቦ ውሳኔ መስጠት ያስችለው ዘንድ ቦርዱ በዛሬው ዕለት ያሳለፈውን ውሳኔ ዝርዝር ለምክር ቤቱ  እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል። ምክር ቤቱ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳቢያ መደበኛ ስብሰባዎቹን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማያደርግ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮ ኢሌክሽን)

Leave a Reply