አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳዎችን የያዘ የዳሰሳ ጥናት ለፓርላማ ተላከ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ምርጫ ሊካሄድባቸው የሚችልባቸውን ሁለት አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳዎችን ያካተተ የዳሰሳ ጥናት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላከ። የጊዜ ሰሌዳዎቹ መጪው ምርጫ በታህሳስ አሊያም በየካቲት የመካሄድ ዕድል እንዳለው ጥቆማ ሰጥተዋል።

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ፤ መጋቢት 22፤ ባወጣው መግለጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፤ የተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል አሳውቆ ነበር። ምክር ቤቱ የስልጣን ጊዜውን አስመልክቶ ውሳኔ የሚያሳልፍ ከሆነ ለዚያ ይረዳው ዘንድ ቦርዱ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ለፓርላማው እንዲተላለፍ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

በ28 ገጾች የተዘጋጀው እና “ኢትዮ ኢሌክሽን” የተመለከተችው ይህ የዳሰሳ ጥናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጪው አጠቃላይ ምርጫ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ የተነተነ ነው። ጥናቱ የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ላይ በመመስረት የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን እና የምርጫ ኦፕሬሽንን ከልሶ፣ ስራውን እንደገና ማስጀመር የሚቻልባቸው አማራጭ የእቅድ አፈጻጸሞችን በዝርዝር አስቀምጧል። በምርጫ ቦርድ አማካሪ ባለሙያዎች ተሰርቶ የቀረበው ጥናቱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶችን በዋናነት አስቀምጧል። 

የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንታት ብቻ እንደሚቆዩ ታሳቢ ያደረገ ነው። እርምጃዎቹ የመራጮች ምዝገባን ቢያንስ በአራት ሳምንታት ሊያዘገዩት እንደሚችሉ ሆኖም ምርጫውን አስቀድሞ በተያዘለት ቀን ማከናወን እንደሚቻል የጠቆመ ነበር። 

ይህ አካሄድ የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከመክተቱም ባሻገር የመራጮች እና አጠቃላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል የዳሰሳ ጥናቱ አመላክቷል። በዚህ ጊዜ ለምርጫ ኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን የተሟላ ድጋፍ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጥናቱ ጠቅሷል። 

ቦርዱ “የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በድጋሚ ግምገማ በማድረግ፣ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድ እና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምር ይሆናል” ሲል በማክሰኞው ውሳኔው ላይ ጠቁሟል።

ሁለተኛው የቢሆን ሁኔታ ግምት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች “ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላም ሊቆዩ ይችላሉ” በሚል የተዘጋጀ ነው። በየጊዜው የሚወሰዱት እርምጃዎች በዚሁ ከቀጠሉ፤ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ምርጫውን ማስፈጸም እንደማይችል ያስጠነቀቀም ነበር። 

ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫ በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ፤ መጋቢት 22፤ ይፋ ያደረገው ውሳኔ ሁለተኛውን የቢሆን ሁኔታ የተንተራሰ ነው። ውሳኔው መጪው ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በታቀደለት ጊዜ መከናወን እንደማይችል ያሳወቀ ነበር። ቦርዱ የዘንድሮውን አጠቃላይ ምርጫ ነሐሴ 23 ለማካሄድ አቅዶ የነበረ ቢሆንም በወረርሽኙ ምክንያት ከወር በፊት ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረዙን ገልጿል። በጊዜ ሰሌዳው የታቀዱ የምርጫ ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙም ውሳኔ አሳልፏል። 

ቦርዱ “የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በድጋሚ ግምገማ በማድረግ፣ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድ እና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምር ይሆናል” ሲል በማክሰኞው ውሳኔው ላይ ጠቁሟል። የዳሰሳ ጥናቱ በበኩሉ የምርጫ ሰሌዳን ለመቀየር እና የምርጫ ተግባራትን ድጋሚ ለማስጀመር፤ የፌደራል እና የክልል የመንግስት ተቋማት ሙሉ የስራ አቅማቸውን የሚያገኙበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ይመክራል።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በፌደራል እና የክልል መንግስታት የተላለፉ ክልከላዎች እና ገደቦች በዝናብ ወቅት የሚነሱ ከሆነ “በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደሚኖር ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የተነሳ ይህን የማከናወኛ ጊዜ ረጅም ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል” ይላል ጥናቱ። ገደቦቹ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት የሚነሱ ከሆነ ወደ ሙሉ ተቋማዊ አቅም ለመመለስ የአንድ ወር የዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አመልክቷል። 

በዚህ የቢሆን እውነታ ላይ በመመርኮዝ በጥናቱ የተካተተ አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ግንቦት 24፤ 2012ን እንደ መነሻ ቀን ወስዷል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጪው ምርጫ በታህሳስ 19 ቀን 2013 መካሄድ ይችላል።

የመራጮች ምዝገባ ከነሐሴ 27 እስከ መስከረም 22፤ 2013 ድረስ መደረግ እንደሚችል የሚጠቁመው ይህ የጊዜ ሰሌዳ የምረጡኝ ዘመቻው ከመስከረም 20፤ 2013 ጀምሮ ባሉት 89 ቀናት ውስጥ እንዲከናወን አማራጭ ሀሳብ አስቀምጧል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምርጫ ቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት እንዲያሳውቅ የሚጠበቀው ከታህሳስ መጨረሻ እስከ ጥር 8፤ 2013 ባሉት ቀናት ይሆናል።

የቦርዱ የዳሰሳ ጥናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የተጣሉት ገደቦች የሚነሱት ከነሐሴ እና እስከ መስከረም ባሉት ወራት ውስጥ ከሆነ በሚል ሌላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳም በአማራጭነት አቅርቧል። በዚህኛው የምርጫ ሰሌዳ መሰረት መራጮች ድምጻቸውን የሚሰጡበት ዕለት የካቲት 21፤ 2013 እንዲሆን ታስቧል።

የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ይፋ የሚደረገው በመጋቢት ወር ባሉት የመጀመሪያ 10 ቀናት ውስጥ ነው። ጥቅምት 24፤ 2013 እንዲጀመር የታቀደው የመራጮች ምዝገባ ክንውን ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን የምረጡኝ ዘመቻ ከህዳር 22 እስከ ጥር 24፤ 2013 ይካሄዳል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየካቲት ወር ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ቢሰርዝም ወደፊት ለሚያወጣው አዲስ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እንዲሁም ምርጫውን ለማስፈፀም የሚደረጉ ዝግጅቶችን ካቆሙበት ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚቆይ በዳሰሳ ጥናቱ ተመልክቷል። ቦርዱ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ለአስቸኳይ ስራ ከሚፈለጉ ሰራተኞች በስተቀር ሌሎች ሰራተኞቹ ከመኖሪያ ቤታችው ሆነው እንዲሰሩ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ውሳኔዎች እስኪተላለፉ ድረስ ቦርዱ በዝቅተኛ አቅሙ ስራዎችን እንደሚያከናውን በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ (ኢትዮ ኢሌክሽን)

One thought on “አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳዎችን የያዘ የዳሰሳ ጥናት ለፓርላማ ተላከ”

Leave a Reply