የህገ መንግስቱ ሶስት አንቀጾች ትርጓሜ እንዲሰጥባቸው በፓርላማ ተወሰነ

የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በዚህ ዓመት የማይካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ፤ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ጸደቀ። የውሳኔ ሀሳቡን 25 የምክር ቤት አባላት ተቃውመውታል።

ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳቡን ያጸደቀው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ባለ የስብሰባ አዳራሽ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 27፤ 2012 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ነው። የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 54 (1)፤ 58 (3) እና 93 ከህገ መንግስት አላማና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆች ጋር ለማስተሳሰር፤ “የህገ መንግስት ትርጓሜ ይሰጥባቸው” የሚል ነው። 

የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 54(1) “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ” ይላል። የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ እና የስራ ዘመንን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን የሚያስቀምጠው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 58 (3) በበኩሉ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል” ሲል ይደነግጋል። 

በቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሀሳብ ትርጓሜ እንዲሰጥባቸው ከተባሉ አንቀጾች የመጨረሻው የሆነው እና በአንቀጽ 93 የተቀመጠው የህገ መንግስት ክፍል ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግግ ነው። በአንቀጽ 93 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው “የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን ነው” ይላል። ከዚህ በተጨማሪም “ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይምን የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌደራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንግግ ሥልጣን አለው” ሲል ያስቀምጣል። 

የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ በጠቀሳቸው በእነዚህ አንቀጾች ላይ በህገ መንግስቱ መሰረት ትርጓሜ መስጠት የሚችለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑ ተገልጿል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ትርጉሙን በአንድ ወር ወስጥ እንዲያደርስ የተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ልዩ ስብሰባው ወስኗል፡፡ (ኢትዮኢሌክሽን)

Leave a Reply