የምርጫ ካርታ በመጪው ወር ይፋ ይደረጋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም በምርጫ ጣቢያነት ያገለገሉ ቦታዎችን ለመለየት የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን እየተጠቀመ ይገኛል። በመስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች የተዘጋጀው የምርጫ ጣቢያዎች ካርታ በቅርቡ ለቦርዱ ውሳኔ ይቀርባል ተብሏል። 

ቦርዱ ነሐሴ 23 ለሚካሄደው ሀገራዊ  ምርጫ እስከ 48 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ የየምርጫ ጣቢያዎቹን ወሰን የመለየት ስራን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለወራት ሲያካሂድ መቆየቱን በቅርቡ ገልጿል። በአዲስ አበባ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን የጂ.ፒ.ኤስ መረጃ ለማሰባሰብ ብቻ 20 ቀናት መውሰዱን የቦርዱ ባለሙያዎች አስረድተዋል። 

ከዘንድሮው ምርጫ በፊት በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ወቅት የምርጫ ክልሎችን እና የምርጫ ጣቢያዎችን የሚገልፅ ካርታ አልነበረም።  የምርጫ ጣቢያዎች የሚታወቁት በስም እና በቁጥር ብቻ እንደነበር ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ይህ አሰራር ምርጫ ለማካሄድ፣ አዳዲስ ምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት እንዲሁም ሎጅስቲክስ እና ቁሳቁስ ለማሰራጨት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ባለሙያዎቹ ያብራራሉ። እነዚህን ችግሮች ይፈታል የተባለለት አዲሱ የምርጫ ካርታ በመጪው የመጋቢት ወር መጀመሪያ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።


የምርጫ የማዘዣ ማዕከል ሊቋቋም ነው

ምርጫ ቦርድ የቀጣዩ ምርጫ ደህንነትን ለማረጋገጥ በራሱ የሚመራ እና 27 አባላት የሚኖሩት የጋራ የምርጫ የማዘዣ ማዕከል (Joint Election Operation Center – JEOC) በፌደራል ደረጃ ለማቋቋም እቅድ እንዳለው አስታውቋል። በእቅዱ ላይ ምክክር ይደረግበታል ተብሏል።

ማዕከሉን የመመስረት እቅድ ይፋ ያደረጉት የምርጫ ቦርድ አባል ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ናቸው። ዶ/ር ጌታሁን የካቲት 6 በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይ እንደተናገሩት ቦርዱ “በምርጫ ሂደት ውስጥ የሚታየው ስጋት (risk) ምንድነው?” የሚለውን የተመለከተ ጥናት በሁለት ዙር አካሂዷል። የዳሰሳ ጥናቱ ወደፊትም በየጊዜው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። 

የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል አለምሸት ደግፌ ባለፈው መስከረም ወር በተደረገ አንድ ኮንፍረንስ ላይ የጸጥታ ጉዳዮችን የሚከታተል የምርጫ ማዕከል የማቋቋም አስፈላጊነትን አንስተው ነበር።  ምርጫው ይሳካ ዘንድ “የምርጫ ጸጥታ ማስከበሪያ ማዕከል” ማቋቋም እንደሚሻል መክረዋል።  

በምርጫ ወቅት ሰላም እና ጸጥታን ለማረጋገጥ መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ገለጻ ያደረጉት ሜጀር ጄነራል አለምሸት በኢትዮጵያ “የጦር መሳሪያ ዝውውር በጣም ከልኩ ያለፈ ነው” ሲሉ አሳሳቢነቱን ጠቅሰዋል። በመጪው ምርጫ የጸጥታ ችግር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ካሏቸው ውስጥ “የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች” ይገኙበታል። የታጠቁ ኃይሎች “ህዝብ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ነጻ ምርጫ የሚባል ነገር ሊደረግ አይችልም” ብለዋል።

በየካቲት 6 ኮንፍረንስ ላይ የተገኙት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ለምርጫ “ሰራዊታችንን በአግባቡ እናሰለጥናለን። የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንዴት መከላከል እንደሚቻል በቂ ዝግጅቶች አድርገናል” ብለዋል። “በከተማም ሆነ በገጠር ሽፍታ ካለ አንቀበልም። ህግ እናስከብራለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ሀገር ውስጥ ገብተዋል

ለቀጣዩ ሀገራዊ  ምርጫ የሚያገለግሉ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች  ተጠናቅቀው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ምርጫ ገልጿል። ሰነዶቹ እና ቁሳቁሶቹ ለ50,800 የምርጫ ጣቢያዎች የሚከፋፈሉ እንደሚሆኑም ጠቁሟል። 

ከምርጫ ጣቢያዎች ሌላ ለስልጠና ብቻ የሚውሉ 4,200 ሰነዶች እና ቁሳቁሶችም እንደዚሁ ተጠቃልለው ሀገር ቤት መድረሳቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።  ምርጫ ቦርድ የካቲት 6 ባለድርሻ አካላትን በጋበዘበት ኮንፍረንስ ላይ በመጋዘን ውስጥ፣ በካርቶን ታሽገው የተከማቹ የመራጮች የምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን ለተሳታፊዎች በቪዲዮ አሳይቷል። 

ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁሶች የተከማቹት ከፍተኛ ጥበቃ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕቃ ማከማቻ መጋዘን መሆኑን ቦርዱ ለዕይታ ባበቃው ቪዲዮ ላይ ተመልክቷል። 

ነሐሴ 23 ለሚካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ ሰነዶች  የታተመው “አል-ጉህሬር” በተባለ በዱባይ በሚገኝ ማተሚያ ቤት ነው። ከሀገር ውጪ ሲካሄድ “የመጀመሪያ ነው” የተባለለትን የምርጫ ቁሳቁሶች ህትመት የተጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር። የምርጫ መዛግብቱ እና ሰነዶቹ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች እንደሚታተሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

የዱባዩ ህትመት የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተዓማኒ ያደርጋል ተብሎለታል።  ህትመቱ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሲከናወን ከነበረው ምን እንደሚለየው ለመረዳት ዝርዝሩን ከስዕላዊ መረጃው ይመልከቱ።  

ቀጣዩ ምርጫ ነሐሴ 23 ይካሄዳል

ለምረጡኝ ዘመቻ ከግንቦት እሰከ ነሐሴ ያለው ጊዜ ተደልድሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የካቲት 6 ይፋ አድርጓል። በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ይሆናል። ቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ይፋ የሚያደርገው ከምርጫው ማግስት አንስቶ እስከ ጳጉሜ 3 እንደሆነ አስታውቋል።

ምርጫ ቦርድ በጥር ባወጣው ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ቀጣዩ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ነሐሴ 10 እንዲሆን ሃሳብ አቅርቦ ነበር። በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የድምጽ መስጫው በ13 ቀናት ወደፊት የተገፋ ሲሆን በሌሎች ክንውኖች ላይም ሽግሽግ ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የድምጽ መስጫ ቀናት የተደለደሉት ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ውስጥ ነበር። ምስሉን ይመልከቱ።