Tag: COVID19

የምርጫ ቦርድ የውጭ ሀገር ሰራተኞች በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጡ በርካታ የውጭ ሀገር ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የመስሪያ ቤቱ ምንጮች ገለጹ። በሀገር ውስጥ የቀሩትም ቢሆኑ በቤታቸው እንዲሰሩ ድርጅቶቻቸው ውሳኔ ማሳለፋቸው ታውቋል። 

ምን ያህል የውጭ ሀገር ሰራተኞች እስካሁን ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ አጠቃላይ መረጃ በመጠናቀር ላይ መሆኑን የተናገሩት የቦርዱ የ“ኢትዮኢሌክሽን” ምንጭ፤ ሆኖም ቁጥራቸው “በርካታ” የሚባል እንደሆነ አስረድተዋል። “የተወሰኑቱ ሀገር ለቅቀው ሄደዋል” የሚሉት እኚሁ ምንጭ “ሌሎቹ ወደ የሀገራቸው የሚወስዳቸው በረራ ለማግኘት በመቸገራቸው አሁንም ለመሄድ በጥረት ላይ ናቸው” ብለዋል። 

ለምርጫ ቦርድ በቀጥታ ስራ ከሚሰሩ ከእነዚህ ቁልፍ ሰራተኞች በተጨማሪ በየዓለም አቀፍ ተቋማቱ   ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑን ለ“ኢትዮኢሌክሽን” የደረሰው መረጃ ያመለክታል። ምርጫ ቦርድም  “አጋሮቼ” ብሎ የሚጠራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በበሽታው ስጋት ምክንያት የየራሳቸውን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ይህን የገለጸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጪው ምርጫ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው የግምገማ ሰነድ ላይ ነው። እርምጃዎቹ ተቋማቱ ለመጪው ምርጫ ሊያበረክቱት በሚችሉት የቴክኒካዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ላይ “ጉልህ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል” ብሏል ሰነዱ።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት “ለኢትዮጵያ ምርጫ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል” ሲል ምርጫ ቦርድ ስጋቱን ገልጿል 

ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ለ45 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ቀርቦ ምክክር በተደረገበት በዚህ ሰነድ ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቦርዱ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ቃል የተገባለትን ገንዝብ የማግኘት ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ተጠቁሟል። “አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ከግምት ከገባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምርጫዎች ድጋፍ የተመደበው ገንዘብ ለሰብዓዊ እና የጤና ድጋፍ የመዛወር እድሉ ከፍ ያለ ነው” በማለት ስጋቱን ያስቀመጠው የቦርዱ ሰነድ “በዚህ ምክንያትም ለኢትዮጵያ ምርጫ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል” ሲል ያስጠንቅቃል። 

ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 እንዲካሄድ ቀን የተቆረጠለትን የዘንድሮ ምርጫ ለማካሄድ 3.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። የፌደራል መንግስት ለቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን እና ሎጀስቲክ ስራ ማከናወኛ የመደበው ገንዘብ ግን 2.25 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ቀሪውን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ ማህብረሰብ በሚገኝ ድጋፍ ለመሸፈን ላቀደው ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የ40 ሚሊዮን ዶላር ያህል የገንዘብ ድጋፍ ቃል ተገብቶለት ነበር።  (ኢትዮኢሌክሽን)