ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሚያገለግሉ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች ተጠናቅቀው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ምርጫ ገልጿል። ሰነዶቹ እና ቁሳቁሶቹ ለ50,800 የምርጫ ጣቢያዎች የሚከፋፈሉ እንደሚሆኑም ጠቁሟል።
ከምርጫ ጣቢያዎች ሌላ ለስልጠና ብቻ የሚውሉ 4,200 ሰነዶች እና ቁሳቁሶችም እንደዚሁ ተጠቃልለው ሀገር ቤት መድረሳቸውንም ጨምሮ አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ የካቲት 6 ባለድርሻ አካላትን በጋበዘበት ኮንፍረንስ ላይ በመጋዘን ውስጥ፣ በካርቶን ታሽገው የተከማቹ የመራጮች የምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን ለተሳታፊዎች በቪዲዮ አሳይቷል።
ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁሶች የተከማቹት ከፍተኛ ጥበቃ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕቃ ማከማቻ መጋዘን መሆኑን ቦርዱ ለዕይታ ባበቃው ቪዲዮ ላይ ተመልክቷል።
ነሐሴ 23 ለሚካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ ሰነዶች የታተመው “አል-ጉህሬር” በተባለ በዱባይ በሚገኝ ማተሚያ ቤት ነው። ከሀገር ውጪ ሲካሄድ “የመጀመሪያ ነው” የተባለለትን የምርጫ ቁሳቁሶች ህትመት የተጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር። የምርጫ መዛግብቱ እና ሰነዶቹ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች እንደሚታተሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የዱባዩ ህትመት የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተዓማኒ ያደርጋል ተብሎለታል። ህትመቱ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሲከናወን ከነበረው ምን እንደሚለየው ለመረዳት ዝርዝሩን ከስዕላዊ መረጃው ይመልከቱ።
