Tag: Prosperity Party

የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ የጸጥታ ሁኔታ ግምገማ ምን ይመስላል?

• ለመጪው ምርጫ በአንድ እዝ ስር የሚሰማራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ሊቋቋም ታስቧል

ለመጪው ምርጫ ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች የሚወከሉበት፣ ኃይሉንም በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች፣ በአንድ እዝ ስር የሚያሰማራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ሊቋቋም እንደሚችል የብልጽግና ፓርቲ ለአመራሮቹ ባሰራጨው ሰነድ ላይ አስታወቀ። በቅድመ ምርጫ ወቅት ይቋቋማል የተባለው ይህ ግብረ ኃይል የሚደራጀው “በዲሞክራሲ ሽግግር የላዕላይ ምክር ቤት” እንደሆነ ሰነዱ ገልጿል።

ገዢው ፓርቲ ይህን እቅድ ይፋ ያደረገው “ሀገራዊ የለውጥ እርምጃዎች” በሚል ርዕስ ለመካከለኛ አመራሮቹ ስልጠና ባዘጋጀው ሰነድ ላይ ነው። ሰነዱ በኢትዮጵያ መጥቷል የሚለውን ለውጥ “ምንነት እና ስኬቶቹን” የሚተነትን ሲሆን በሀገር ደረጃ ያጋጥማሉ ያላቸውን “ቀጣይ ፈተናዎች እና መሻገሪያ ስልቶችን” ያመላክታል። በ174 ገጾች በተዘጋጀው በዚህ ሰነድ ማገባደጃ ላይ የ2012ቱ ሃገራዊ ምርጫ ጉዳይም ተዳስሷል።

ከምርጫ ዝግጅት እስከ ድህረ ምርጫ ያሉ ሂደቶችን በ11 ገጾች የተመለከተው የፓርቲው ሰነድ በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያላቸውን ተግዳሮቶች በዝርዝር አስቀምጧል። ሰነዱ “የመንጋ አደረጃጀቶች” ሲል የሚጠራቸው ኃይሎች የምርጫውን ሂደት ሊያውኩ እንደሚችሉ ደጋግሞ ያስጠነቅቃል።

የገዢው ፓርቲ ሰነድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ላይ ሊፈጥሩት ስለሚችሉት እንቅፋት በምሳሌ በማስደገፍ አብራርቷል። “የጎበዝ አለቆች” እና “ያኮረፉና ቀልባሽ ኃይሎች” ተብለው በሰነዱ የተገለጹ አካላትም በምርጫ ወቅት ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።  

ፓርቲው በእነዚህ እና ሌሎች ቡድኖች የሚፈጠሩ ችግሮችን የመቆጣጠር ከፍተኛ ኃላፊነት የጣለው በጸጥታ ኃይሉ ላይ ነው። “በፍትጊያ በሚሞላው የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተለይም ፉክክሩ እየጋመ በሚሄድበት የቅስቀሳው የመጨረሻ ቀናት የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማት አቅም እጅግ የሚፈተንበት ይሆናል። የጸጥታ ኃይሉም በልዩ ሁኔታ የሚወጠር ይሆናል” ሲል ሰነዱ ይተነብያል። 

የጸጥታ ኃይሎች “ምርጫውን ለማሰናከል እና ተዓማኒነቱን ለማጉደፍ በሚሹ ያኮረፉና ቀልባሽ ኃይሎች የሚዶለቱ ውስብስብ የወንጀል ሴራዎችን ማክሽፍ” እንደሚጠበቅባቸው የብልጽግና ፓርቲ ሰነድ ያሳስባል። 

የጸጥታ ኃይሎች “በተመሳሳይ ሰዓት ለሚካሄዱ መርሃ-ግብሮች ጥበቃ ከማድረግ አንስቶ፣ ምርጫውን ለማሰናከል እና ተዓማኒነቱን ለማጉደፍ በሚሹ ያኮረፉና ቀልባሽ ኃይሎች የሚዶለቱ ውስብስብ የወንጀል ሴራዎች፣ ችግር ከመፍጠራቸው በፊት ማክሽፍ ይጠበቅባቸዋል” ሲል ሰነዱ አስቀድመው ማድረግ የሚገባቸውን ይጠቁማል። “የወንጀል መከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን የጸጥታ መዋቅሩን አቅም እስከ መጨረሻው አሟጦ መጠቀም ይገባል” ሲልም ይመክራል።

መጪዎቹ ወራት “ነገሮች በፍጥነት የሚለዋወጡበት፤ ፉክክርና ፍትጊያ መገለጫዎቹ” እንደሚሆኑ የሚተነብየው የብልጽግና ፓርቲ ሰነድ በዚህ ወቅት የሚከሰተውን ውጥረት “ፈጥኖ መቆጣጠር” እንደሚያሻም ያሳስባል። ሰነዱ “እጅግ ስስ የሆነ ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ” ሲል ለሚጠራው ለዚህ ወቅት በመፍትሄነት ያስቀመጠው በአንድ እዝ ስር የሚሰማራ የፀጥታ ግብረ ኃይልን ነው።

“በተሳታፊ ፓርቲዎች ነጻነቱ የሚረጋገጥ ይሆናል” የተባለለት ይህ የፀጥታ ግብረ ኃይል ከክልሎች እና ከዞን አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተገልጿል። ግብረ ኃይሉ በቅድመ ምርጫው ወቅት “የስጋት ቀጠናዎችን” የመለየት ተልእኮ የሚሰጠው ሲሆን “ስርዓተ አልበኝነትን የሚያስፋፉ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶችን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት” ኃላፊነትም ተጥሎበታል። 

ለግብረ ኃይሉ የተሰጠው ሌላው ኃላፊነት ስምምነት የተደረሰባቸውን የምርጫ ቃል ኪዳን ሰነዶችን የሚጥሱ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “እንዲታረሙ” ማድረግ ነው። “ከምርጫ ቦርድ ጋር በትብብር በመስራት” ይፈጸማል የተባለው “የእርምት እርምጃ” ምንነት ግን በሰነዱ ላይ አልተብራራም። 

የገዢው ፓርቲ ሰነድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከቱ ግምገማዎቹን በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ወቅት ከፋፍሎ አስቀምጧል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከምርጫ ከማግለል አንስቶ ሁከት እስከመፍጠር የደረሰ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ያስጠንቅቃል። 

“በምርጫ ፉክክር ወቅት የሚፈልጉትን አጀንዳ እንደማይሳካ የተረዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው በማግለል ህዝቡን በምርጫ እንዳይሳተፍ ሊቀሰቅሱት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በምርጫው ዕለት በመንጋ ሁከት በመፍጠር ህዝቡ ከቤት እንዳይወጣ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በመክፈት በምርጫ እንዳይሳተፍ ሊያደናቅፉት ይጥራሉ”

የብልጽግና ፓርቲ ሰነድ

“በምርጫ ፉክክር ወቅት የሚፈልጉትን አጀንዳ እንደማይሳካ የተረዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው በማግለል ህዝቡን በምርጫ እንዳይሳተፍ ሊቀሰቅሱት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በምርጫው ዕለት በመንጋ ሁከት በመፍጠር ህዝቡ ከቤት እንዳይወጣ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በመክፈት በምርጫ እንዳይሳተፍ ሊያደናቅፉት ይጥራሉ” ይላል ሰነዱ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ ምርጫ ወቅት ነገሮች በሰላማዊ መንገድ እንዳይሄዱ ጋሬጣዎች ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ሰነዱ ያትታል። “አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች የምርጫውን ቃል ኪዳን ሰነድ ስምምነት አለማክበር፣ በምርጫው ውጤት አለመስማማት እና ከቦርዱ ውሳኔ በፊት አሸንፌያለሁ በማለት የተደራጁ ኃይሎችን ሰላማዊ ሰልፍ [ሊያስወጡ] ይችላሉ” ሲል ጋሬጣዎቹን ዘርዝሯል። የፖለቲካ ኃይሎቹ “አሸናፊነታቸውን ለመግለጽ በተለያዩ የአመጻ ተግባራት ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ” ሲልም ይተነብያል።

“ውጤቱን የማይቀበሉ ኃይሎች ህዝቡን ሁከት እና ግርግር ውስጥ፣ የተደራጀ የብሄር ግጭት ውስጥ፣ በመንጋ አደረጃጀትና በፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፎች ውስጥ ሊከቱት ከመቻላቸው ባሻገር ውጤት ሳይገለጽ በጊዜያዊ ውጤት እኛ አሸንፈናል በሚል መግለጫ ሊያደናግሩት ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የሚጎዱት በግጭት ውስጥ የሚሳተፈውን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ የማይሆነውን ህዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴም ሊገቱት ይችላሉ” የሚለው የብልጽግና ፓርቲ ሰነድ የተለያዩ ወገኖች ማድረግ አለባቸው ያላቸውን ነገሮች ጠቁሟል።  

የብልጽግና ፓርቲ፤ ምርጫውን የተመለከቱ አቅጣጫዎች የሰፈሩበትን ይህን ሰነድ፤ 40 ሺህ ገደማ ለሚሆኑ መካከለኛ አመራሮቹ ያሰራጨው ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ነበር።

“በምርጫው ውጤት የማይስማሙ ቡድኖች ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው ገለልተኛ አካል በማቅረብ የሚሰጠውን ውሳኔ በፀጋ እንዲቀበሉ ሊደረግ ይገባል” የሚለው ሰነዱ የጸጥታ አካላት በዚህ ረገድ ማከናወን የሚገባቸውን አመላክቷል። “ተዓማኒ ምርጫ ፍጹም በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ የፖለቲካና የጸጥታ አውድ መደረግ የሚኖርበት በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የጸጥታ ኃይሎች ምርጫውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ድርጊቶችን በልዩ ንቃት ሊከተሉና አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል” ሲል ሰነዱ አሳስቧል።

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ፤ ምርጫውን የተመለከቱ አቅጣጫዎች የሰፈሩበትን ይህን ሰነድ፤ 40 ሺህ ገደማ ለሚሆኑ መካከለኛ አመራሮቹ ያሰራጨው ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ነበር። ሰነዱ በክልሎች እና በአዲስ አበባ ደረጃ ላሉ የፓርቲው መካከለኛ አመራሮቹ በተሰጠ የ10 ቀናት ስልጠና ወቅት በግብዓትነት ከዋሉ ጥራዞች አንዱ ነበር። (ኢትዮኢሌክሽን)