Tag: Election2012

አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳዎችን የያዘ የዳሰሳ ጥናት ለፓርላማ ተላከ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ምርጫ ሊካሄድባቸው የሚችልባቸውን ሁለት አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳዎችን ያካተተ የዳሰሳ ጥናት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላከ። የጊዜ ሰሌዳዎቹ መጪው ምርጫ በታህሳስ አሊያም በየካቲት የመካሄድ ዕድል እንዳለው ጥቆማ ሰጥተዋል።

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ፤ መጋቢት 22፤ ባወጣው መግለጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፤ የተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል አሳውቆ ነበር። ምክር ቤቱ የስልጣን ጊዜውን አስመልክቶ ውሳኔ የሚያሳልፍ ከሆነ ለዚያ ይረዳው ዘንድ ቦርዱ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ለፓርላማው እንዲተላለፍ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

በ28 ገጾች የተዘጋጀው እና “ኢትዮ ኢሌክሽን” የተመለከተችው ይህ የዳሰሳ ጥናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጪው አጠቃላይ ምርጫ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ የተነተነ ነው። ጥናቱ የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ላይ በመመስረት የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን እና የምርጫ ኦፕሬሽንን ከልሶ፣ ስራውን እንደገና ማስጀመር የሚቻልባቸው አማራጭ የእቅድ አፈጻጸሞችን በዝርዝር አስቀምጧል። በምርጫ ቦርድ አማካሪ ባለሙያዎች ተሰርቶ የቀረበው ጥናቱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶችን በዋናነት አስቀምጧል። 

የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንታት ብቻ እንደሚቆዩ ታሳቢ ያደረገ ነው። እርምጃዎቹ የመራጮች ምዝገባን ቢያንስ በአራት ሳምንታት ሊያዘገዩት እንደሚችሉ ሆኖም ምርጫውን አስቀድሞ በተያዘለት ቀን ማከናወን እንደሚቻል የጠቆመ ነበር። 

ይህ አካሄድ የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከመክተቱም ባሻገር የመራጮች እና አጠቃላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል የዳሰሳ ጥናቱ አመላክቷል። በዚህ ጊዜ ለምርጫ ኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን የተሟላ ድጋፍ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጥናቱ ጠቅሷል። 

ቦርዱ “የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በድጋሚ ግምገማ በማድረግ፣ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድ እና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምር ይሆናል” ሲል በማክሰኞው ውሳኔው ላይ ጠቁሟል።

ሁለተኛው የቢሆን ሁኔታ ግምት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች “ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላም ሊቆዩ ይችላሉ” በሚል የተዘጋጀ ነው። በየጊዜው የሚወሰዱት እርምጃዎች በዚሁ ከቀጠሉ፤ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ምርጫውን ማስፈጸም እንደማይችል ያስጠነቀቀም ነበር። 

ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫ በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ፤ መጋቢት 22፤ ይፋ ያደረገው ውሳኔ ሁለተኛውን የቢሆን ሁኔታ የተንተራሰ ነው። ውሳኔው መጪው ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በታቀደለት ጊዜ መከናወን እንደማይችል ያሳወቀ ነበር። ቦርዱ የዘንድሮውን አጠቃላይ ምርጫ ነሐሴ 23 ለማካሄድ አቅዶ የነበረ ቢሆንም በወረርሽኙ ምክንያት ከወር በፊት ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረዙን ገልጿል። በጊዜ ሰሌዳው የታቀዱ የምርጫ ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙም ውሳኔ አሳልፏል። 

ቦርዱ “የወረርሽኙ ስጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በድጋሚ ግምገማ በማድረግ፣ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድ እና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምር ይሆናል” ሲል በማክሰኞው ውሳኔው ላይ ጠቁሟል። የዳሰሳ ጥናቱ በበኩሉ የምርጫ ሰሌዳን ለመቀየር እና የምርጫ ተግባራትን ድጋሚ ለማስጀመር፤ የፌደራል እና የክልል የመንግስት ተቋማት ሙሉ የስራ አቅማቸውን የሚያገኙበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ይመክራል።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በፌደራል እና የክልል መንግስታት የተላለፉ ክልከላዎች እና ገደቦች በዝናብ ወቅት የሚነሱ ከሆነ “በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደሚኖር ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የተነሳ ይህን የማከናወኛ ጊዜ ረጅም ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል” ይላል ጥናቱ። ገደቦቹ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት የሚነሱ ከሆነ ወደ ሙሉ ተቋማዊ አቅም ለመመለስ የአንድ ወር የዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ጥናቱ አመልክቷል። 

በዚህ የቢሆን እውነታ ላይ በመመርኮዝ በጥናቱ የተካተተ አማራጭ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ግንቦት 24፤ 2012ን እንደ መነሻ ቀን ወስዷል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጪው ምርጫ በታህሳስ 19 ቀን 2013 መካሄድ ይችላል።

የመራጮች ምዝገባ ከነሐሴ 27 እስከ መስከረም 22፤ 2013 ድረስ መደረግ እንደሚችል የሚጠቁመው ይህ የጊዜ ሰሌዳ የምረጡኝ ዘመቻው ከመስከረም 20፤ 2013 ጀምሮ ባሉት 89 ቀናት ውስጥ እንዲከናወን አማራጭ ሀሳብ አስቀምጧል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምርጫ ቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት እንዲያሳውቅ የሚጠበቀው ከታህሳስ መጨረሻ እስከ ጥር 8፤ 2013 ባሉት ቀናት ይሆናል።

የቦርዱ የዳሰሳ ጥናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የተጣሉት ገደቦች የሚነሱት ከነሐሴ እና እስከ መስከረም ባሉት ወራት ውስጥ ከሆነ በሚል ሌላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳም በአማራጭነት አቅርቧል። በዚህኛው የምርጫ ሰሌዳ መሰረት መራጮች ድምጻቸውን የሚሰጡበት ዕለት የካቲት 21፤ 2013 እንዲሆን ታስቧል።

የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ይፋ የሚደረገው በመጋቢት ወር ባሉት የመጀመሪያ 10 ቀናት ውስጥ ነው። ጥቅምት 24፤ 2013 እንዲጀመር የታቀደው የመራጮች ምዝገባ ክንውን ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን የምረጡኝ ዘመቻ ከህዳር 22 እስከ ጥር 24፤ 2013 ይካሄዳል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየካቲት ወር ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ቢሰርዝም ወደፊት ለሚያወጣው አዲስ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እንዲሁም ምርጫውን ለማስፈፀም የሚደረጉ ዝግጅቶችን ካቆሙበት ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚቆይ በዳሰሳ ጥናቱ ተመልክቷል። ቦርዱ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ለአስቸኳይ ስራ ከሚፈለጉ ሰራተኞች በስተቀር ሌሎች ሰራተኞቹ ከመኖሪያ ቤታችው ሆነው እንዲሰሩ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ውሳኔዎች እስኪተላለፉ ድረስ ቦርዱ በዝቅተኛ አቅሙ ስራዎችን እንደሚያከናውን በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ (ኢትዮ ኢሌክሽን)

መጪው ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በታቀደለት ጊዜ እንደማይካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት መጪውን አጠቃላይ ምርጫ ማድረግ የማይችል መሆኑን አስታወቀ። የተወካዮች ምክር ቤት ሁኔታውን ተገንዝቦ ውሳኔ እንዲያሳልፍም ጠይቋል።

ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በምርጫ 2012 ኦፕሬሽን ላይ የፈጠረውን ችግር ከገመገመ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ ባለፈው የካቲት ወር ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረዙን ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳው የታቀዱ ተግባራትም ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑንም ገልጿል።

በቦርዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲሆን ታቅዶ ነበር። ቦርዱ ከምርጫው ማግስት አንስቶ እስከ ጳጉሜ 3 ድረስ የተረጋገጠ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ በጊዜ ሰሌዳው ማስቀመጡ ይታወሳል።

በተለምዶ በግንቦት ወር ይካሄድ የነበረው አጠቃላይ ምርጫ ወደ ነሐሴ ወር የተገፋው በአዲስ አወቃቀር እና አባላት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመጪው ምርጫ “በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዲያገኝ” በሚል ነበር። ምርጫው በክረምት ወር እንዲደረግ መወሰኑን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። 

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ መጪውን ምርጫ ከነሐሴ ወር ወዲያ ባሉት ጊዜያት ለማከናወን የማይችለው በኢትዮጵያ ህገ መንግስት በተቀመጠ ገደብ ምክንያት መሆኑን ምላሽ ሰጥቶ ነበር። ቦርዱ በዛሬው መግለጫውም ይህን የህገ መንግስት የጊዜ ገደብ አንስቷል። 

በስራ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ መጪውን አጠቃላይ ምርጫ ማድረግ እንደሚኖርበት መግለጫው አስታውሷል። ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት እንዳያከናውን ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል። በዚህም ምክንያት ምርጫውን በእቅዱ መሰረት ማድረግ እንደማይችል አስታውቋል።

የተወካዮች ምክር ቤት አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቦ ውሳኔ መስጠት ያስችለው ዘንድ ቦርዱ በዛሬው ዕለት ያሳለፈውን ውሳኔ ዝርዝር ለምክር ቤቱ  እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል። ምክር ቤቱ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳቢያ መደበኛ ስብሰባዎቹን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማያደርግ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮ ኢሌክሽን)

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተባባሰ በመጪው ምርጫ ዕጣ ፈንታ ላይ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ችግር ለተራዘመ ጊዜ የሚቀጥል ከሆነ እና በምርጫ ቦርድ ስራ ላይ እንቅፋት ከፈጠረ የመጪው ምርጫን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ውይይት እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ዛሬ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ነው። 

የኮሮና ቫይረስ በመጪው ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር እንደው ለመለየት ምርጫ ቦርድ የራሱን ጥናት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቦርዱን ጥናት መሰረት አድርጎ ውሳኔ እንደሚተላለፍ አመልክተዋል። የመጨረሻ ውሳኔው ይፋ የሚደረገውም “የጋራ ስምምነት” ከተደረሰበት በኋላ እንደሚሆን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ “በሰበር ዜና” በተላለፈው መግለጫቸው አስታውቀዋል። 

“በቻይና እንዳየነው አይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄንን ጉዳይ መቆጣጠር፣ ማለፍ የሚቻል ከሆነ በአሰብነው እቅድ መሰረት መሄዱ ተመራጭ ቢሆንም ምናልባት ለተራዘመ ጊዜ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ እና ምርጫ ቦርድ ስራውን መከወን የሚቸገር ከሆነ፤ በሚያደርጉት ጥናት መሰረት ውይይት የሚደረግ ይሆናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ “በሰበር ዜና” በተላለፈው መግለጫቸው የኮሮና ቫይረስ በምርጫ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የራሱን ጥናት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  የቦርዱን ጥናት መሰረት አድርጎም ውሳኔ እንደሚተላለፍ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ለሳምንታት አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማረጋገጫ ሰጥቷል። ምርጫ ቦርድ በቫይረስ ምክንያት ተጽዕኖ ሊደርስባቸው ያላቸው “ከፍተኛ የሰው ዝውውር ያሳትፋሉ” በሚል የገለጻቸውን “የመራጮች ትምህርት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እና የቁሳቁስ ስርጭትን” ነው። 

በእነዚህ ተግባራት ላይ የሚደርስ መስተጓጎል በመራጮች ምዝገባ ዝግጅት ላይ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ቦርዱ ዛሬ ለውይይት ለጠራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጻ አድርጓል።  ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተሳተፉበት በተገለጸው በዚህ ውይይት የኮሮና ቫይረስ በምርጫ ኦፕሬሽን ስለሚኖረው ተጽዕኖ እና ሊወሰዱ ስለሚችሉ አማራጭ እርምጃዎች ውይይት መደረጉን ቦርዱ አስታውቋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  በምርጫው ዝርዝር አፈጻጸም እና በጊዜ ሰሌዳው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመገምገም፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተከታታይ ውይይት በቀጣይም እንደሚያደርግ ቦርዱ ገልጿል። (ኢትዮኢሌክሽን) 

የአውሮፓ ህብረት ለመጪው ምርጫ የታዛቢ ቡድን እንደሚልክ ማረጋገጫ ሰጠ

የአውሮፓ ህብረት ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ምርጫ የታዛቢዎች ቡድን እንደሚልክ አስታወቀ። ህብረቱ የታዛቢ ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ ዛሬ ማረጋገጫ የሰጡት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ናቸው። 

ከአፍሪካ ህብረት ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ከ20 የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነሮች ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጡት ቦሬል ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋርም ተገናኝተዋል። በአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችን እና የጸጥታ ፖሊሲን በኃላፊነት የሚመሩት ቦሬል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከተነሱ አንኳር ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የምታካሄደው ምርጫ ይገኝበታል።  

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከውይይቱ በኋላ በግል የትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን እና መረጋጋትን ለማጠናከር መጪው ምርጫ ሁነኛ መፈተሻ ነው” ብለዋል። በዚሁ መልዕክታቸውም የህብረቱ ታዛቢ ቡድን በመጪው ነሐሴ የሚካሄደውን ምርጫ እንደሚታዘብ ይፋ አድርገዋል። 

የአውሮፓ ህብረት የዘንድሮውን ምርጫ እንዲታዘብ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ታህሳስ ወር ይፋዊ ግብዣ እንደደረሰው ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ይህንን ተከትሎም ህብረቱ የቅድመ ምርጫ ጥናት ቡድን ባለፈው ወር ወደ ኢትዮጵያ ልኳል። ቡድኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ለሁለት ሳምንታት ጥናት ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር ተነጋግሯል። 

የቅድመ ምርጫ ጥናት ቡድኑ በሀገሪቱ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ መገምገሙን ቡድኑን መርተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ሎይክ ዲፋዬ ገልጸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የሎጀስቲክ እና የትራንስፖርት ጉዳዮችን መመልከታቸውን አስረድተዋል። ዲፋዬ “የታዛቢዎች ቡድንን በተመለከተ ዋናው መሰረታዊ መስፈርት የቡድኑ ጠቃሚነት ነው። ለመጪው ምርጫ ተጨማሪ እሴት ይኖረዋልን?” ሲሉ “ቁልፉ ነገር ሂደቱ” መሆኑን አጠይቀው ነበር። 

የምርጫ ካርታ በመጪው ወር ይፋ ይደረጋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም በምርጫ ጣቢያነት ያገለገሉ ቦታዎችን ለመለየት የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን እየተጠቀመ ይገኛል። በመስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች የተዘጋጀው የምርጫ ጣቢያዎች ካርታ በቅርቡ ለቦርዱ ውሳኔ ይቀርባል ተብሏል። 

ቦርዱ ነሐሴ 23 ለሚካሄደው ሀገራዊ  ምርጫ እስከ 48 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ የየምርጫ ጣቢያዎቹን ወሰን የመለየት ስራን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለወራት ሲያካሂድ መቆየቱን በቅርቡ ገልጿል። በአዲስ አበባ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን የጂ.ፒ.ኤስ መረጃ ለማሰባሰብ ብቻ 20 ቀናት መውሰዱን የቦርዱ ባለሙያዎች አስረድተዋል። 

ከዘንድሮው ምርጫ በፊት በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ወቅት የምርጫ ክልሎችን እና የምርጫ ጣቢያዎችን የሚገልፅ ካርታ አልነበረም።  የምርጫ ጣቢያዎች የሚታወቁት በስም እና በቁጥር ብቻ እንደነበር ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ይህ አሰራር ምርጫ ለማካሄድ፣ አዳዲስ ምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት እንዲሁም ሎጅስቲክስ እና ቁሳቁስ ለማሰራጨት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ባለሙያዎቹ ያብራራሉ። እነዚህን ችግሮች ይፈታል የተባለለት አዲሱ የምርጫ ካርታ በመጪው የመጋቢት ወር መጀመሪያ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።


የምርጫ የማዘዣ ማዕከል ሊቋቋም ነው

ምርጫ ቦርድ የቀጣዩ ምርጫ ደህንነትን ለማረጋገጥ በራሱ የሚመራ እና 27 አባላት የሚኖሩት የጋራ የምርጫ የማዘዣ ማዕከል (Joint Election Operation Center – JEOC) በፌደራል ደረጃ ለማቋቋም እቅድ እንዳለው አስታውቋል። በእቅዱ ላይ ምክክር ይደረግበታል ተብሏል።

ማዕከሉን የመመስረት እቅድ ይፋ ያደረጉት የምርጫ ቦርድ አባል ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ናቸው። ዶ/ር ጌታሁን የካቲት 6 በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይ እንደተናገሩት ቦርዱ “በምርጫ ሂደት ውስጥ የሚታየው ስጋት (risk) ምንድነው?” የሚለውን የተመለከተ ጥናት በሁለት ዙር አካሂዷል። የዳሰሳ ጥናቱ ወደፊትም በየጊዜው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። 

የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄነራል አለምሸት ደግፌ ባለፈው መስከረም ወር በተደረገ አንድ ኮንፍረንስ ላይ የጸጥታ ጉዳዮችን የሚከታተል የምርጫ ማዕከል የማቋቋም አስፈላጊነትን አንስተው ነበር።  ምርጫው ይሳካ ዘንድ “የምርጫ ጸጥታ ማስከበሪያ ማዕከል” ማቋቋም እንደሚሻል መክረዋል።  

በምርጫ ወቅት ሰላም እና ጸጥታን ለማረጋገጥ መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ገለጻ ያደረጉት ሜጀር ጄነራል አለምሸት በኢትዮጵያ “የጦር መሳሪያ ዝውውር በጣም ከልኩ ያለፈ ነው” ሲሉ አሳሳቢነቱን ጠቅሰዋል። በመጪው ምርጫ የጸጥታ ችግር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ካሏቸው ውስጥ “የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች” ይገኙበታል። የታጠቁ ኃይሎች “ህዝብ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ነጻ ምርጫ የሚባል ነገር ሊደረግ አይችልም” ብለዋል።

በየካቲት 6 ኮንፍረንስ ላይ የተገኙት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ለምርጫ “ሰራዊታችንን በአግባቡ እናሰለጥናለን። የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንዴት መከላከል እንደሚቻል በቂ ዝግጅቶች አድርገናል” ብለዋል። “በከተማም ሆነ በገጠር ሽፍታ ካለ አንቀበልም። ህግ እናስከብራለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ሀገር ውስጥ ገብተዋል

ለቀጣዩ ሀገራዊ  ምርጫ የሚያገለግሉ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች  ተጠናቅቀው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ምርጫ ገልጿል። ሰነዶቹ እና ቁሳቁሶቹ ለ50,800 የምርጫ ጣቢያዎች የሚከፋፈሉ እንደሚሆኑም ጠቁሟል። 

ከምርጫ ጣቢያዎች ሌላ ለስልጠና ብቻ የሚውሉ 4,200 ሰነዶች እና ቁሳቁሶችም እንደዚሁ ተጠቃልለው ሀገር ቤት መድረሳቸውንም ጨምሮ አስታውቋል።  ምርጫ ቦርድ የካቲት 6 ባለድርሻ አካላትን በጋበዘበት ኮንፍረንስ ላይ በመጋዘን ውስጥ፣ በካርቶን ታሽገው የተከማቹ የመራጮች የምዝገባ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን ለተሳታፊዎች በቪዲዮ አሳይቷል። 

ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁሶች የተከማቹት ከፍተኛ ጥበቃ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕቃ ማከማቻ መጋዘን መሆኑን ቦርዱ ለዕይታ ባበቃው ቪዲዮ ላይ ተመልክቷል። 

ነሐሴ 23 ለሚካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ ሰነዶች  የታተመው “አል-ጉህሬር” በተባለ በዱባይ በሚገኝ ማተሚያ ቤት ነው። ከሀገር ውጪ ሲካሄድ “የመጀመሪያ ነው” የተባለለትን የምርጫ ቁሳቁሶች ህትመት የተጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር። የምርጫ መዛግብቱ እና ሰነዶቹ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች እንደሚታተሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

የዱባዩ ህትመት የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተዓማኒ ያደርጋል ተብሎለታል።  ህትመቱ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሲከናወን ከነበረው ምን እንደሚለየው ለመረዳት ዝርዝሩን ከስዕላዊ መረጃው ይመልከቱ።  

ቀጣዩ ምርጫ ነሐሴ 23 ይካሄዳል

ለምረጡኝ ዘመቻ ከግንቦት እሰከ ነሐሴ ያለው ጊዜ ተደልድሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የካቲት 6 ይፋ አድርጓል። በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ይሆናል። ቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ይፋ የሚያደርገው ከምርጫው ማግስት አንስቶ እስከ ጳጉሜ 3 እንደሆነ አስታውቋል።

ምርጫ ቦርድ በጥር ባወጣው ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ቀጣዩ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ነሐሴ 10 እንዲሆን ሃሳብ አቅርቦ ነበር። በይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የድምጽ መስጫው በ13 ቀናት ወደፊት የተገፋ ሲሆን በሌሎች ክንውኖች ላይም ሽግሽግ ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የድምጽ መስጫ ቀናት የተደለደሉት ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ውስጥ ነበር። ምስሉን ይመልከቱ።